መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ
የመንበር ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአዲስ አበባ ከተማ፣ አራት ኪሎ ሰፈር የሚገኝ ቤተክርስቲያን ነው። የቅድስት ስላሴ የመሠረት ድንጋይ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፲፱፻፳፬ ዓ/ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲያስቀምጡ የእስክንድርያ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ እና የሀገር ጳጳሳትም በተገኙበት ልዩ ጸሎት እና ቡራኬ ተሠጥቶ ተመረቀ።
ቤተክርስቲያኑ በመጀመሪያ ዙር ልዩ መልክ ባለው እቅድ ተገንብቶ በሮችን መገጣጠምና ጌጣ ጌጥ ነገሮችን ማስገባት ሲቀር በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ ለመውረር ስለተነሳ ሥራው መቆም ግድ ሆነበት። የፋሺስት ኢጣልያም ጠቅላላ ኃሣብ የኢትዮጵያን ሙሉ ክብር ፈጽሞ ለመግፈፍ እና የእራሱን አሻራ ለማላከክ ስለነበር፣ የዚህን ካቴድራል የአሠራር ጥራት እና የቦታውንም አቀማመጥ ምቹነት በመገንዘብ የካቶሊክ ካቴድራል ለማድረግ ወሰነ። ሆኖም በግድ እና በግፍ ወሰደው ላመባል ግምቱን ሰጥቶ መውሰድን መርጦ የጊዜውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በማስፈራራት ግምት ከፍዬ ልውሰደው ሲል ጠየቃቸው። ያገኘው መልስ ግን «ዛሬ መብቱ ያንተ ነው። በግድ ለመውሰድ ትችላለህ፤ ግን በፈቃዳችን አናደርገውም» የሚል ቆራጥ መልስ በመሆኑ፣ እጠላት እጅ ሳይገባ ቀረ።
በ
፲፱፻፴፫ ዓ/ም በተገኘው ድል ንጉሠ ነገሥቱ ሲመለሱ፣ የሕንፃው ሥራ እንደገና ተጀምሮ በቅልጥፍና ተሠርቶ ካለቀ በኋላ “መንበረ ፀባዖት” ተብሎ በቅድስት ሥላሴ ስም ተሰይሞ
ጥር ፯ ቀን
፲፱፻፴፮ ዓ/ም፤ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሊቃውንት፣ የሴት ወይዛዝር፣ የጦር ሠራዊት በተገኙበት ተመረቀ። ካቴድራሉ መታሰቢያነቱም በ፭ቱ የጠላት ወረራ ዓመታት ለተዋጉት አርበኞች ሆነ። ቅዳሴ ቤቱ ከተባረከ በኋላ በባህር የተጣሉትን፤ በገደል የወደቁትን እና በማይታወቅ ቦት የረገፉትን አርበኞች ዐጽም ተሰብስቦ በዚሁ ዕለት በልዩ የጸሎት ሥነ ሥርዓትና በታላቅ የሰልፍ አጀብ ተቀበረ።